ህዳር 5 2001ዓም>>>
የኮንታ ልዩ ወረዳ የመንግስት ሰራተኞች በሥራ ላይ የሚታዩ መሰረታ ችግሮችን ለማስወገድ ውጤታማ ሥራ ለመስራት መዘጋጀታቸው ተገለጸ፡፡ ልማት ዲሞክራሲና አቢዮታዊ ዲሞክራሲ እንዲሁም ልማት በሲቪል ሰርቫንቱ ጥያቄ ምን ይመስላል በሚል ርዕስ የሴክተሮች ዕቅድና ፓኬጆች ላይ ለ8 ተከታታይ ቀናት አጠቃላይ ለመንግስት ሰራተኞች ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከትላንት በስቲያ ተጠናቋል፡፡ በስልጠናው የተገኙት አጠቃላይ የሲቪል ሰርቫንቱ ብዛት 347 ሲሆን ወንድ 234 ሴት 113 ናቸው፡፡ የስልጠናው ተካፋይ የሆኑት አቶ አያሌው ከበደ እና ዶማንኮ ዶላንጎ ከስልጠናው ቡኃላ እንደገለጹት ለልማታችን እንቅፋት የሆነ የአፈጻጸም ችግሮች በማስወገድ ስልጠናው ትልቅ ፋይዳ አለው ካሉ ቡኃላ ከስልጠናው ባገኘነው ግንዛቤ በስራችን ላይ የሚታዩ መሰረታዊ ችግሮችን አስወግደን ውጤታማ ስራ ለመስራት ተዘጋጅተናል ሲሉም ገልፀዋል ፡፡ እንዲሁም ልማት በሲቪል ሰርቫንቱ ጥያቄ ምን ይመስላል በሚል ርዕስ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና የቀበሌ ስራ አስኪያጆች ለ6 ተከታታይ ቀናት የቆየ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳደር አቶ ሽብሩ እሸቱ እንደገለጹት እያንዳንዱ የመንግስት ሰራተኞች መልካም አስተዳደርን በማረጋገጥ ፈጣን ዘላቂ ልማት በማምጣት የህዝብ አገልጋይነትን መንፈስ በተላበሰ መልኩ ለሃገር ዕድገት መረባረብ አለበት ብለዋል ፡፡ የአቅም ግንባታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታዬ ተሰማ በበኩላቸው በወረዳው የሚገኙ የሴክተር መ/ቤቶች ሰራተኞች ዕቅዳቸውን መሰረት አድርገው ስራቸውን መተግበር እንዳለባቸውና በስልጠናው ያገኙት ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡